Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ አየር ኃይል አመራሮች የፓናል ውይይት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ አየር ኃይል አመራሮች እና የአቪዬሽን አገልግሎት የሚሰጡ የውጭ ድርጅቶች ያካሄዱት የፓናል ውይይት ተጠናቀቀ።

በፓናል ውይይቱ ማጠቃለያ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ በፓናሉ ለተሳተፉ ሀገራትና ለአቪዬሽን ድርጅቶች ስጦታ አበርክተዋል።

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት÷ አየር ኃይል ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ እራሱን እያሳደገ የመጣ ተቋም ነው።

አየር ኃይሉ ቀደም ብሎ የታጠቃቸው ትጥቆች ለኪሳራ የሚዳርጉ እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ላይ ትጥቆችን ዘመኑ ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ጋር በማሳደግ የውጊያ ዝግጁነቱን አረጋግጧል ብለዋል።

አየር ኃይሉ አሁን ለደረሰበት ደረጃ አመራሩና አባላቱ ተቀናጅተው መሥራታቸው የጋራ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው÷ አመራሩ የተፈጠረውን አቅም የበለጠ ለማሳደግ ተግቶ መስራት ይጠበቅበታልም ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ሀገራት አየር ሃይሎች ችግሮቻቸውን በጋራ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ÷ በስልጠና እና በቴክኒክ ያሉ የትብብር ድጋፎች ሊጠናከሩ ይገባል ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

አየር ኃይሉ የተመሰረተበት 88ሻ ዓመት “በመሥዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

Exit mobile version