Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ኅብረተሰቡን ያሳተፉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተገለጸ ።

ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም እየጠበቀ ልማቱን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረና የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮች እንዲሁም የኢሉባቦር ዞንና የመቱ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት መድረክ በመቱ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ የአስተዳደር፣ ፀጥታና ፍትሕ ዘርፍ አስተባባሪ ኮሚሽነር ከፊያለው ተፈራ በዚሁ ወቅት÷በክልሉ የሕግ የበላይነትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው ስራ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።

ሰላምና ልማት ተለያይተው መታየት የሌለባቸው የሕልውና ጉዳዮች እንደመሆናቸው በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እኩል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዞኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወኑ በሚገኙት ሰላምን የማስጠበቅ ስራ መልካም አርአያ ነው ያሉት ደግሞ የኢሉባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ተደራጅተውና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ሰላማቸውን በማረጋገጡ ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡና ልማቱን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ገልፀዋል።

Exit mobile version