Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከበረታን፣ ከተዘጋጀን፣ አንድ መሆናችንን ለውስጥም ለውጭም ካሳየን አንደፈርም – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከበረታን፣ ከተዘጋጀን፣ አንድ መሆናችንን ለውስጥም ለውጭም ካሳየን አንደፈርም ብቻ ሳይሆን የሚሞክሩ ካሉም ለመግታት እራሳችንን ለመከላከል ያግዘናል ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ አብዝቶ የሰለጠነ በቀላሉ ማሸነፍ ይችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ነጻነት መጥተው ሊገዳደሩ የሚፈልጉ ኃይሎች የማድረግ አቅማችን አይተው እንዲገቱ፤ ከሞከሩም እንዲቀጡ ማድረግ ነውና በስልጠና የዳበረ ብቃትን መፍጠር ከሁላችን የሚጠበቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለየትኛውም ኃይል አትበገርም፣ ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አያውቅምም ብለዋል፡፡

ዛሬን መገንባት ያስፈለገው ኢትዮጵያን የማጽናት ታሪካዊ ሀላፊነት ስላለብን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ አዲስ መንገድ መጀመር ፈተና እንደሚገጥመው ጠቅሰው÷ ነገር ግን የጀመርነውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚደረጉ ትናንሽ ሙከራዎችን ሳንመለከትና ምላሽ ሳንሰጥ ወደ ፊት መገስገስ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ሁለተኛውን ወረራ ስታውጅ ኢትዮጵያ በወቅቱ ያልነበራትን አየር ኃይል በመጠቀም ጥቃት በመክፈቷ ቁጭት ማሳደሩንና አየር ኃይል መቋቋሙን አስታውሰዋል።

አየር ሀይሉ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ የተለያዩ ሀገራትና የአየር ኃይል ሙያተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ጀግኖች አባቶች የመሠረቱትን አዘምኖ በማስቀጠል ጠንካራ ሀገርና ተቋም መገንባታችንን እንቀጥላለንም ነው ያሉት፡፡

ጋብቻቸውን በአየር ኃይሉ የምስረታ ቀን በዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ለፈጸሙ ሁለት ወጣቶች እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል፡፡

አየር ኃይሉ ያሰለጠናቸው አብራሪዎች፣ የበረራ አስተማሪዎች፣ ቴክኒሺያኖችና የነገ የአየር ኃይል መሪ ኦፊሰሮችን አስመርቋል።

Exit mobile version