Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የተገኘው ሰላም ህዝቡን የማሳተፍ ውጤት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አሁን ላይ የተገኘው ሰላም በሕግ ማስከበሩ ሂደት ህዝቡን በማሳተፍ የመጣ ውጤት መሆኑ ተገለጸ።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀሪ ወራት አቅጣጫ ዙሪያ በባሕርዳር ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንዳሉት÷ በክልሉ አጋጥሞ የነበረውን የሰላም ማጣት ችግር በመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ድጋፍ መቀልበስ ተችሏል።

በዚህም በክልሉ አብዛኛው አካባቢ ሰላም በማስፈን ወደ ልማት ለመሸጋገር እድል እየተፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የመንግስት ሰራተኛው፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲሳካ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የቀረበውን የሰላም ጥሪ ብዙዎቹ እየተጠቀሙበት መሆኑንና በቀሪ ቀናት ሌሎችም በተመሳሳይ መተግበራቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ልማቱ እንዲፋጠን ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል ።

ባለፉት ወራት ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታት የውይይት መድረኮች እየተካሄዱ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version