Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት 936 ተጠርጣሪዎች ስልጠና በመውሰድ ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት 936 ተጠርጣሪዎች ምክርና የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላት በሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ለሁለተኛ ዙር በጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በመጎብኘት ከአመራሩም ጋር ውይይት አድርገዋል።

በጉብኝታቸውም የተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ መልካም መሆኑም ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት የዘመቻ ሃላፊ ኮሎኔል መንገሻ ፈንታው እንደገለፁት÷ ኮማንድ ፖስቱ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሰራ ነው።

በቀጣናው 779 ተጠርጣሪዎች በሦስት ዙር የተሃድሶ ስልጠና ወስደው እንዲሁም 157 ተጠርጣሪዎች በምክር ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ 936 ተጠርጣሪዎች በሦስት ዙር የተሃድሶ ስልጠና በምክር ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውንም ነው የተናገሩት።

የጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ አስተባባሪ አቶ በሪሁን ተገኝ በበኩላቸው÷ አሁን በቁጥጥር ስር ውለው ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች መካከል 152 የሚሆኑት የተሃድሶ ትምህርት በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎች በስነምግባር ታንጸው ወጥተው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ አስፈላጊው ትምህርት እና ተሃድሶ እየተሰጠ እንደሆነ መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ነጃት ግርማ (ዶ/ር) ÷ ተጠርጣሪዎች መልካም የሚባል የሰብዓዊ መብት አያያዝ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የምግብ፣ የመኝታ፣ የንጽሕና መጠበቂያ እና ከዘመድ ጋር የመገናኘት ሁኔታቸው ጥሩ መሆኑን ከተጠርጣሪዎች ማረጋገጣቸውንም ነው የተናገሩት።

በጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በሰጡት አስተያየትም ሰብዓዊ መብት አያያዝ በኩል ምንም ዓይነት መጓደል አለመኖሩን አስረድተዋል።

Exit mobile version