አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ተጠየቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በሩሲያ የማዕድን ሃብት ኤጀንሲ ኃላፊ ኢቭጌኒ ፔትሮቭ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ለሩሲያ ባለሃብቶች ልዑክ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለፃ ተደርጓል።
ሀገሪቱ ለኢንዱስትሪ ምቹ ሥነ-ምኅዳር እንዲሁም በቂ የሰው ኃይልና የጥሬ ዕቃ ዕምቅ ዐቅም እንዳላት አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮ-ሩሲያን ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ በሣይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በማዕድንና ኢነርጂ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ እንድታጋራ ጠይቀው፤ የሀገሪቱ ባለሃብቶች ምቹ የአምራች ኢንዱስትሪ ምኅዳር መኖሩን ተገንዝበው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገች መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡
ኢቭጌኒ ፔትሮቭ በበኩላቸው÷ የሩሲያ ባለሃብቶች ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም በተለይም በሣይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የማዕድንና ኢነርጂ ሃብቷን ለዘላቂ ልማት እንድታውል÷ የሥነ-ምድር አሰሳ የጥናት ዐቅሟን እንድታሣድግ ሩሲያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

