Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 8 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረጉት የበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን እና ወረታ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ናቸው።

የቢ ኬ ጂ ፋውንዴሽን የ7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን÷ ወረታ ኢንተርናሽናል ደግሞ የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር)፥ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች ተቋማትም መሰል ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በገንዘቡ የምግብ ዕህል ተገዝቶ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግኸምራ እና በደብረብረሃን መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች ይዳረሳል ተብሏል።

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ አሁን ላይ በክልሉ ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች የዕለት ምግብ ድጋፍ እንደሚጠብቁ ተገልጿል።

በወንድሙ አዱኛ

 

Exit mobile version