አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደው በ2ኛው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባኤ ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጓን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ገለጸ።
ኢትዮጵያ በጉባኤ የነበራትን ተሳትፎ በተመለከተ የስደተኞችና ተመላሽ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ደስታ በሰጡት መግለጫ ÷ ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመራ ልዑክ በጉባኤው ተሳትፋለች ብለዋል።
ልዑኩ ጉባኤው በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን ተጠቃሚነት ለማረገጋጥ እያከናወነች ያለውን ተግባራት እንዳቀረበና ከዚህ ጎን ለጎንም የተለያዩ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ስኬታማ ታሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተጓዳኝም ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ተጽዕኖ፣ ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፣ ከትምህርትና ሥልጠና፣ ስደተኞች የሚገኙባቸው ኢንቨስትመንት እድሎች፣ ከስደተኞችና ተቀባይ ማኅበረሰብ ምርታማነት እንዲሁም ከበይነ-መረብ ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ስድስት ቃል ኪዳኖችን ማጽደቋን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከኔዘርላንድስ መንግሥት የ67 ሚሊየን ዩሮ እንዲሁም ከዓለም ባንክ 50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ሥምምነት ማድረጓን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጉባኤውም የስደተኛ ተቀባይ ሀገራትን ጫና ለመቀነስ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ቃል ተገብቷል ተብሏል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ከ26 ሀገራት የተሰደዱ 1 ሚሊየን ስደተኞች እያስተናገደች ትገኛለች።

