አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውድድር ስነ ልቦና እንደዘርፉ ባለሙያዎች ትንታኔ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
ውድድር ሰዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ለማነሳሳት እንደሚረዳና አውጥተውም እንዲያሳዩበት እድል የሚፈጥር መሆኑ ይነገራል፡፡
ሆኖም የውድድር መንፈስ እንደጥቅሙ ሁሉ በትክክል መያዝ ካልተቻለ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡
ጤናማ ያልሆነ ውድድርም የተለያዩ የጤና እክሎችን እንደሚያስከትልም ነው የሚነገረው፡፡
የስነ-ልቦና አማካሪ ባርኮት ጌቱ የውድድር ስነ-ልቦናን አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የውድድር ስነ-ልቦና ሰዎች በህይወታቸው ያልተመለከቱትን አቅጣጫ የሚመለከቱበት እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ መንገዶች የተሻለ ለመሆን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል የስለ-ልቦና አማካሪዋ ባርኮት፡፡
ውድድር አሸናፊና ተሸናፊዎች ያሉበትና ሽንፈትን ፈጽሞ አለመቀበል ራስን አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ሲከት ይታያል፡፡
ከቤተሰብ ወይም ከጓደኛ አልያም በስራ ከባቢ የበዛ የውድድር መንፈስ ሲታይ ተመልክተው ይሆናል፡፡
ይህ የውድድርና የአሸናፊነት ጥማት የሌሎችን ስኬት ዕውቅና ከመንፈግ ጀምሮ የራስን ማንነት አለመቀበል ሊያስከትል እንደሚችልም ይገለጻል፡፡
ይህም ሰዎችን መዋሸት፣ ጫናዎች፣ ጭንቀት፣ የበታችነት ስሜት መሰማትና በቂ ነገር የለኝም በማለት ያሉበትን ቦታ አለመውደድ እና የማንነት ቀውስ ውስጥ እንደሚያስገባም ነው የስነ-ልቦና አማካሪዋ የገለጹት፡፡
ያለአግባብ የውድድር መንፈስ በራስ መተማመን የሚያመጣው ስሜት እንደሆነ ገልጸው፥ የራሴ ነገር በቂ አይደለም በሚል ሃሳብ ሌሎችን ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡
ይህ ስሜት እየቆየ ሲሄድም ቁጣ፣ ንዴት፣ ቅናት እና መሰል ስሜቶች መገለጥ ይጀምራሉ ብለዋል የስለ-ልቦና አማካሪዋ፡፡
ይህ ስሜት ከየት እንደመነጨ ማስተዋል፣ የሰዎችን ስኬት መቀበል፣ የውድድሩ ፍላጎት ራስን ከማሳደግ የመነጨ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው የሚለውን መለየት ችግሩን በወቅቱ ለመፍታት እንደሚያግዝም ይነገራል፡፡