Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ375 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ375 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 189 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 186 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የወጭ በድምሩ 375 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፎች መያዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሐኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዋሽ፣ ድሬዳዋ እና ጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፎች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 111 ሚሊየን፣ 74 ሚሊየን እና 66 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ እንደቻሉ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በብርበራና በጥቆማ የተያዙ ናቸው ተብሏል፡፡

ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 19 ተጠርጣሪዎች እና ስድስት ተሽከርካሪዎችን መያዝ እንደተቻለ ተጠቅሷል፡፡

ድርጊቱን ለመግታትና ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Exit mobile version