አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አበባን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቶችን በካርጎ ጭነት ወደ ውጭ ገበያ እያጓጓዘ መሆኑን አስታወቀ።
በዓለም አገራት የተስፋፋው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ መገደቡን ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች እንቅስቃሴያቸውን በማቆም ሠራተኞቻቸውን አያሰናበቱ ይገኛሉ።
ከዚያም ባለፈ አየር መንገዶች ከመንግስታቸው ከፍተኛ የሆነ ድጎማ እየጠየቁ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በአሁኑ ወቅት የወረርሽኙን ተጽዕኖ ለመቋቋም በመንገደኞች ያጣውን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ለማግኘት ፊቱን ወደ ካርጎ አገልግሎት አዙሯል።
በዚህም በርካታ የሰብዓዊ እና ሌሎች የነፍስ አድን ድጋፎችን ለአህጉሪቷ አፍሪካና ሌሎች የዓለም ክፍሎች እያደረሰ ይገኛል።
በተጨማሪም አየር መንገዱ ይህን ክፉ አጋጣሚ ወደ መልካም በመቀየር የካርጎ አገልግሎቱን ለኢንዱስትሪ ፓርክ ላኪ ድርጅቶች የዋጋ ቅናሽ በማድረግ የአበባና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ እስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ÷ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በገጠመው ተግዳሮት ሳይበገር ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በካርጎ አገልግሎቱ የሚሰጡ የሰብዓዊ ድጋፎችን ከማጓጓዝ ጎን ለጎን አበባን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ወደ ውጭ በማጓጓዝ ገበያ የማፈላለግ ሥራም እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በአፍሪካ ቁጥር አንድ የአበባ አምራችና ላኪ የነበረችው ኬንያ ትጠቀም የነበረው የአውሮፓ አየር መንገዶችን እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ሥራ በማቆማቸው በአገሪቱ ያሉ ላኪዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመጠቀም ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
“በኢኮኖሚው መስክ ለመደጋገፍ ሲባል በኢትዮጵያ ለሚገኙት ላኪዎች ቅድሚያ በመስጠት እየሰራን ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው የአበባ ምርት ብቻ በቀን ከ200 ቶን በላይ ኤክስፖርት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈታሚው አያይዘውም የረመዳን የጾም ወቅትን ተከትሎ በርካታ የሥጋ ምርት ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኩንም አስረድተዋል።
አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ከካርጎ አገልግሎት 15 በመቶ፣ ከመንገደኞች ደግሞ 85 በመቶ ገቢ ያገኝ እንደነበር አስታውሰው÷ በአሁኑ ወቅት ከመንገደኞች የሚገኘው ገቢ በመቆሙ የካርጎ አገልግሎቱ ወደ 30 በመቶ ማደጉ ተገልጿል።
“የካርጎ አገልግሎት ገቢው የበፊቱን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ባይተካ እንኳ ድርጅቱ የገጠመውን ችግር ተቋቁሞ የሠራተኞችን ደመወዝና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን እንዲሁም የአውሮፕላኖቹን እዳ ለመክፈል ያስችላል” ነው አቶ ተወልደ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሌሊሴ ነሚ በበኩላቸው÷ የኢንቨስተሮች የምርት እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ተናግረዋል።
“ይህንን ለመደገፍና አምራቾች ወደ ሥራ እንዲገቡ በአየር መንገዱ በኩል እስከ ስድስት ወር የሚቆይ የማጓጓዣ ቅናሽ መደረጉ ትልቅ ማበረታቻ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

