በ2011 ዓ.ም በወርሃ ግንቦት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ አበባን ለከተማ ለቱሪስቶች ሳቢ፣ ማራኪና አመቺ ለማድረግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ገቢ ለማስገኘት የሚያስችል የ”ገበታ ለሸገር” መርሐ ግብርን አዘጋጁ።
መርሐ ግብሩ ከተካሄደ በኋላ በሚገርም ፍጥነት የሸገር እና የእንጦጦ ፓርኮች ተጠናቀው ለጎብኚዎች ክፍት ሲደረጉ የመዲናዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ ክስተት ሆነ። ብዙዎች በመዲናዋ ውበት ከመደመም አልፈው ፕሮጀክቶቹ የተሰሩበት ፍጥነትና የፕሮጀክቶቹ አመራር ላይ ያላቸውን አድናቆት አልሸሸጉም።
የፕሮጀክቶቹ ወደ ስራ መግባት በርካታ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከማስቻል ባለፈ የከተማይቱም ገጽታ መቀየር እንደሚቻል በማሳየት በቀጣይ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ መንገድ ጠርጓል።
እነዚህ ተግባራት የፈጠራ ክህሎት መነቃቃትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓላማ ያላቸውን ዕቅድ አቅዶ የማስፈጸም ዓቅም ታይቶባቸዋል።
ከሁሉም በላይ ትክክለኛ አመራር ካለ በውጤታማነት በመጓዝ ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማድረስ የሚያስችሉትን የኢትዮጵያን የተትረፈረፉ ሀብቶች የሚያመላክቱ ተምሳሌታዊ ማሳያዎች ሆነዋል።
በዚህም የፕሮጀክት ሀሳቡ አመንጪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “ገበታ ለሀገር” የተሰኘ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይፋ በማድረጋቸው ከቤት እስከ ሀገር ለሚደረገው ብልጽግና ከ”ገበታ ለሸገር” ውጤታማነት በመነሳት ሌሎች ፕሮጀክቶችን በህዝብ ተሳትፎ በማጀብ ውጤታማ ለማድረግ የታለመ መርሀ ግብር ተጀመረ፡፡
ይህ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የመጀመሪያው ዙር ከአዲስ አበባ ውጪ ሶስት ቦታዎችን ከአማራ ክልል ጎርጎራ፣ ከኦሮሚያ ክልል ወንጪ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮይሻን ለማልማት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ ለመሆን ተችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሥራውን የሚመራና የሚያስተባብር ከመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተውጣጣ ኮሚቴም በማዋቀር ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ሀላፊነት እንዲወስዱ ማድረጋቸው ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ፕሮጀክቶቹን ተፈጻሚ ለማድረግ ከማኅበረሰቡ የሚጠበቀው የገንዘብ ድጋፍ በጥቅሉ ከገበታ ለሃገር ቢያንስ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡