Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምስረታ መርሐ-ግብር በሆሳዕና ከተማ በዛሬው ዕለት ተካዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የክልሉ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ÷ መደጋገፍ፣ መፈቃቀድና መቻቻል የሚሰፍንበት፤ አብሮነት፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም የነገሠበት ክልል እየገነባን ነው ብለዋል።

ክልሉ የተለያዩ ሐይማኖቶችና እምነቶች በጋራ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩበት፣ የሐይማኖት አባቶች የሚመክሩበት ከመሆኑ በሻገር የሠላምና የመቻቻል ተምሳሌት ጭምር ነው ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው÷ ጉባዔው በሐይማኖታዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ የሠላምን ዕሴት በመገንባትና አብሮነትን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እንዲጠበቅ የማድረግ ታላቅ መንፈሳዊና ሀገራዊ ተልኮውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ሁሉም ሐይማኖቶች በሰዎች መካከል ሰላማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖር በአፅንኦት ያስተምራል ያሉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ÷ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስለሠላም ተግተው እንዲያስተምሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ሐይማኖቶች እና እምነቶች የሚገኙ ሲሆን÷ የሁሉንም ሐይማኖቶች አስተምህሮ ማክብር ይገባል ሲሉ ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version