አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከዓለም ንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሺያንግቺን ዛህንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያከናወነቻቸው በሚገኙ ሥራዎች ላይ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረቻቸውን ሥራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኗን አንስተዋል፡፡
አምባሳደር ሺያንግቺን ዛህንግ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎችንና ለሒደቱ ያሳየችውን ቁርጥኝነት ማድነቃቸውን በጄኔቫ የኢትዮያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል።
የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የሚከናወኑ ሒደቶች ውስብስብ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል የምታደረገው ጉዞ አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ÷አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በጄኔቫ የስራ ጉብኝት ከማድረጋቸው ጎን ለጎን ከዓለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጊልበርት ኤፍ ሁንግቦ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ ዓለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት የሰራተኞችን መብት በማስከበርና ጥሩ የስራ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር እየሰራ ያለው ስራ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
የዓለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጊልበርት ኤፍ ሁንግቦ በበኩላቸው ÷ ዓለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት በኢትዮጵያ ለሚሰራው ስራ ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀው÷ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ባደረገቻቸው ስምምነቶች የስራና የሰራተኛ መብትን በማስከበር ረገድ የተመዘገቡት ድሎች የሚደነቁ ናቸውም ብለዋል፡፡