Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለዲጂታል ኢንዱስትሪ ልማት የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ እንድትሆን የማድረግ አቅም አለው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለዲጂታል ኢንዱስትሪ ልማት የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ በዘርፉ ተወዳዳሪ እንድትሆን የማድረግ አቅም እንዳለው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

በዲጂታል ኢንዱስትሪ ‘’አውትሶርስ’’ ተደርገው በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የሚመክር መድረክ በዘርፉ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት ÷በዲጂታል ኢንዱስትሪ የ”አውትሶርሲንግ’’ ሥራ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ በመሆኑ መንግስትም ለዘርፉ ልማት በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ዘርፉ በተጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው ÷ ዘርፉ ካለው ሰፊ ዕድል አኳያ ገና ያልተነካና ለኢትዮጵያ በርካታ ዕድሎችን ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው ÷ ቀድመን ወደ ዘርፉ ባለመግባታችን ሰፊ የሥራ ዕድል እና ብዙ የውጭ ምንዛሬ አምልጦናል ብለዋል፡፡

አክለው እንደገለጹት ፥በተጀመረ በአጭር ጊዜ የተመዘገበው ለውጥ የሚያሳየው በትክክለኛ ፖሊሲና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር ከሰራን ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ጸጋ ለመጠቀም ሰፊ ዕድል አለ፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ‘‘አውትሶርስ’’ የተደረጉ ዓለም አቀፍ ሥራዎች ወስደው በብቃት ሰርተው እንዲያስረክቡ ምቹ ሁኔታ የመፍጠርና ተግዳሮቶችንም ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version