Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብልጽግና ፓርቲ ‘ከዕዳ ወደ ምንዳ’ በሚል መሪ ሃሳብ በአባላት ደረጃ ስልጠና እየሰጠ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ) ብልጽግና ፓርቲ ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮቹ ‘ከዕዳ ወደ ምንዳ’ በሚል መሪ ሃሳብ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በአባላት ደረጃም መቀጠሉ አስታውቋል፡፡

ሀገር አቀፍ የስልጠና መርሀ ግብሩ መንግስታዊ የመሪነት አቅምን ለማሳደግ ጉልህ ሚና አበርክቷል ብሏል ፓርቲው።

በዛሬው እለትም ለፌደራል ብልፅግና ዞን አባላት የሚሰጠው ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል።

በመክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው በገዢ ትርክት ግንባታ ዙሪያ ስልጠና የሰጡት የብልፅግና ፓርቲ ህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ÷እንደ ሀገር በትርክት ግንባታ ዙሪያ በርካታ ፈተናዎች እንዳጋጠሙ ገልፀዋል፡፡

“አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሂደት የተፈተንባቸውን ፈተናዎች ድል መንሳት እንድንችል የብሔራዊነት ትርክትን መምረጣችን ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት” ሲሉ መግለፃቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ትርክቶች የሚቀረፁበትና የሚሰራጩበትን መንገድ በማጥናት፣ ነጠላ ትርክቶችና ገዢ ትርክቶች ያላቸውን ልዩነት በመገንዘብ እንዲሁም እንደ ሀገር ያለንን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የብሔራዊነት ትርክት ሀሳብን ለማዳበር እንደተሞከረም ጠቅሰዋል።

እንደ ብልፅግና ፓርቲም አሰባሳቢ እና ብዝሀነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ያስታረቀ ትርክት ፍሬ ያፈራ ዘንድ ሰፊ ስራ በመስራት ላይ እንደምንገኝና አባላትም የበኩላቸውን ድርሻ የሀሳቡን ቀናኢ ፍሬ ተገብዝበው እንዲያበረክቱ አስገንዝበዋል።

ስልጠናው ለተከታታይ 4 ቀናት እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን ÷ በፓርቲው መዋቅር ውስጥ ጠንካራ የሃሳብና የተግባር አንድነት ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

Exit mobile version