አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተከናወኑ የህግ-ማስከበርና የአመራር መልሶ ማደረጃት ስራዎች ክልሉ ወደ ተጨባጭ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲገባ ማስቻላቸው ተገለጸ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የአምስት ወራት ስራ አፈጻጸሙን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ÷ የመከላከያ ሰራዊትና ህዝቡ በመቀናጀት በሰሩት ስራ ክልሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት በእጅጉ መሻሻሉን ገልጸው በክልሉ ተደቅኖ የነበረው አደጋም ሙሉ በሙሉ መቀልበሱን እና የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደገና በማደራጀት ወደተሟላ ተልዕኮ ማስገባት መቻሉን ነው የተናገሩት።
በነበረው ሁኔታ ተደናግረው ከጽንፈኛ ቡድኑ ጋር ተሰልፈው የነበሩ ወጣቶችም ወደ ትክክለኛ መንገድ በመመለስ ከመንግስት ጎን በመሆን ሰላምን የማጽናት ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፥ ባለፉት አምስት ወራት በሶስት ዙሮች ከ20 ሚሊየን በላይ የክልሉ ህዝብ ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ጊዜ የማይሰጣቸው የህዝብ ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በበኩላቸው በአማራ ክልል የጽንፈኛ ቡድኑ ላይ በተደረገ የህግ ማስከበር ተግባር ቡድኑ መዳከሙን አንስተዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ህግ ማስከበር ዘመቻውን ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው በተሳሳተ ቅስቀሳ ወደ ጽንፈኛ ቡድኑ የተቀላቀሉ ወጣቶችም በመመለስ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የሚሰሩ ተግባራትን አጠናቆ መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በሁሉም ቀጠና ኮማንድ ፖስት የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት የተገኘባቸው በመሆኑ ይህን ውጤት በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡