አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁለት ቀን የሚቆይ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መርሐግብር በፓኪስታን ካራቺ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በኤክስፖ ላይ የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን ፥ በውስጡ የኢትዮጵያ የጎብኚ መዳረሻዎች፣ ዘርፈ ብዙ ባህል፣ ታሪክ እና ወደር የለሽ የቱሪዝም መስህቦች የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ እና በፓኪስታን መካከል ያለውን ዘላቂ ትስስርም የሚያሳይ ነው መባሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዛሬው ዕለት የፓኪስታን የፌደራል ትምህርት እና ሙያዊ ስልጠና ሚኒስትር ማዳድ አሊ ሲንዲ የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ባህላዊ የቡና ሥነ ስርዓት የታደሙ ሲሆን፥ አስደናቂ የባህል ትርኢቶችን እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪዝም መስህቦችን በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሠሩ እና በመሠራት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በቪዲዮ ተመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ለማሳደግ እና በዘርፋ ከፓኪስታን ጋር ትስስር ለመፍጠር እያደረገች ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፥ በሀገራቱ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመፍጠር እና የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ኤምባሲው በከፍተኛ ተነሣሽነት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በፓኪስታን ተቀማጭነታቸውን ባደረጉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሠብ፣ በፓኪስታን የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ በሀገሪቱ እና ዓለም አቀፍ የንግድ ማህበረሰብ እና የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን እየጎበኙ ነው።