Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የአንጎል የደም ስር “ክሊፒንግ” በስኬት ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው ነው የተባለለት የአንጎል የደም ስር “ክሊፒንግ” በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ተገለጸ፡፡

ሕክምናው የተደረገላቸው ታካሚ ድንገት በዕለት ሥራቸው ላይ ሳሉ ከፍተኛ የራስ ሕመም ይሰማቸው እንደነበረና ከዚያም እራሳቸውን ስተው መውደቃቸውን የህክምና ታሪካቸው ያስረዳል።

ሕክምና ተቋም እንደደረሱም በተደረገላቸው ምርመራ በአንጎላቸው ውስጥ የደም ቧንቧ መፈንዳት ምክንያት የደም መፍሰስ እንደተከሰተና የፈነዳውን የደም ቧንቧ በቀዶ ጥገና ሕክምና ባስቸኳይ ካልተስተካከለ ለሞት የሚዳርጋቸው እንደነበረም ተነግሯል።

በሆስፒታሉ “በኒውሮሰርጀሪ” ዲፓርትመንት አስተባባሪነትና የአንጎል ደም ቧንቧ ቀዶ ጥገና ሕክምና ከፍተኛ ልምድ ባካበቱት ዶክተር ቶማስ ቦጋለ የተመራ የሕክምና ቡድን ባካሄደው ቀዶ ህክምና ታካሚዋ የተስተካከለ የአንጎል የደም ዝውውር እንዲኖራቸው ማድረግ እንደተቻለ ተገልጿል፡፡

ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የተካሄደው ይህ የተሳካ ቀዶ ህክምና ሶስት ሰዓት ተኩል መፍጀቱም ተነግሯል።

ከዶክተር ቶማስ በተጨማሪ ዶክተር መሃሪ፣ ዶክተር ፒኔል፣ ዶክተር ዳዊት፣ ዶክተር ብዙአየሁ፣ ነርስ ኢብራሂም፣ ሲስተር ሶስና እና ሲስተር መንበረ፣ እንዲሁም ዶክተር ቦንሳ፣ ዶክተር ማህደር፣ ዶክተር እየሩስ፣ ዶክተር ውበት የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች በሂደቱ መሳተፋቸው ተጠቅሷል፡፡

ሕክምናው ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ደረጃ በመንግስት ሆስፒታሎች ሲሰራ የመጀመሪያው መሆኑንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ታካሚዋ በተደረገላቸው ሕክምና እንደተደሰቱ በመግለጽ ባሁኑ ወቅት ከሕመማቸው አገግመው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ተብሏል፡፡

Exit mobile version