Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጋምቤላና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሰላምና ልማት ትብብር ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሰላምና የልማት ትብብር የጋራ ፎረም ተመሰረተ፡፡

የጋራ ፎረሙ ምስረታ መርሐ ግብር የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በምስረታው የትብብር ፎረሙ የሚከተላቸው መርሆች፣ የትብብሩ ተፈፃሚነት ወሰን፣ አደርጃጀቶች፣ ተግባርና ሃላፊነት እንዲሁም ተጠያቂነትን ጨምሮ ሌሎች ዝርዝር ተግባራት ይፋ ሆነዋል።

አቶ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ወቅት እንደገለፁት÷ሁለቱ ክልሎች በፍቅርና በመቻቻል እንዲሁም በትብብር መስራት ከቻሉ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ደረጃ ያሻሽላሉ።

ክልሎቹ ከዚህ በፊት ይከሰቱ የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት ወደ ልማት እንዲገቡ የተደረገበት መንገድ ክልሎቹን የሚያስመሰግን እንደሆነም ገልፀዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ቀደም ሲል የነበረውን ሁለንተናዊ ትብብር በሕግ ማዕቀፍ ማስገባቱ አዋጭ መሆኑን ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ፎረሙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሕጋዊ መስመር በማስያዝ በጋራ የሚሰራበት ነው ማለታቸውንም የጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version