አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ320 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ ኢብራሂም መሃመድ (ዶ/ር)÷ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ወራት በህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች አማካኝነት ከትርፍ አምራች ስፍራዎች እጥረት ወዳለባቸው አካባቢዎች ምርት በመውሰድ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል።
እስካሁንም ከ330 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና እና ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ የኢንዱስትሪ ምርት እንዲሁም ከ2 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለህብረተሰቡ መቅረቡን አንስተዋል።
አምራችና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበት በከተሞች የእሁድና ጊዜያዊ ገበያ ጭምር በማመቻቸት የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከ320 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ በተከናወነው የገበያ ማረጋጋት ሥራም የምርት ዋጋ መሻሻል እንዳሳየ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ገበያውን ከማረጋጋት በተጓዳኝም በህገ ወጥ መንገድ ምርት በሚያከማቹ፣ ዋጋ በሚጨምሩና ሌሎችም የኑሮ ውድነቱን በሚያባብሱ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተሰወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡