Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የገናና የጥምቀት በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የገና፣ የጥምቀት እና ሌሎች በዓላት ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በክልሉ በታኅሣስ መጨረሻ ቀናት እና ጥር ወር ላይ የሚከበሩ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህ መሰረትም በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎች በተዋረድ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይም የገናን በዓል በላሊበላ፣ የጥምቀት በዓልን በጎንደርና ምንጃር ሸንኮራ፣ የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓልን በእንጅባራ፣ የጊዮን በዓልን በሰከላ እንደዲሁም ጥርን በባህርዳር በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በክልሉ የሚከበሩ በዓላትን ለመታደም ለሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የቱሪስት መስህቦችን ለማስጎብኘት በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች አስፈላጊው መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው መደረጉን ነው ያብራሩት ፡፡

ከጸጥታ አንጻርም በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ከክልሉ ጸጥታ አካላት እና ኮማንድ ፖስቱ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አረጋግረጠዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ እንደሁልጊዜው ቀና ትብብር እንደሚያደርግ አውስተው÷ እንግዶች በዓላቱን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ አስተማማኝ ዝግጅት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞም ለበዓል ታዳሚዎች በቂ አገልግሎት ለመስጠት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለበዓላቱ ታዳሚዎች አስፈላጊውን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብም ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ማህበረሰቡ እና አስጎብኚ ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም አንስተዋል፡፡

ስለሆነም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በአማራ ክልል ለሚከበሩ በዓላት በሁሉም ዘርፍ አስተማማኝ ዝግጅት መደረጉን በመገንዘብ ያለምንም ስጋት በበዓላቱ እንዲታደሙ አቶ ጣሂር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version