አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁሉንም ዜጎች ኢኮኖሚ ያገናዘበ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡
የክልሉ የ2016 በጀት ዓመት ክልል አቀፍ የጤና መድኅን የንቅናቄ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የዜጎችን ኢኮኖሚ ያገናዘበ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተግባራዊነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
የአገልግሎቱን ተግባራዊነት በማጠናከርም የሁሉንም ዜጎች ኢኮኖሚ ያገናዘበ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ይሠራል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው÷ የሀገሪቱን ዜጎች ያሳተፈ የጤና ልማት ሥራ በመተግበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዕቅድ ተነድፎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የጤና መድኅን አባላትን ቁጥር በማሣደግ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆንም በየደረጃው ያለው አመራር በትኩረት እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡