Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር 54 ሺህ 288 ወገኖች ከጎዳና መነሳታቸውን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎዳና የሚገኙ ወገኖችን ለማንሣት እንደ ሀገር እስካሁን በተከናወነው ሥራ የተነሺዎች ቁጥር ከነበረበት 39 ሺህ 82 ወደ 54 ሺህ 288 ከፍ ማለቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመትም 19 ሺህ 756 ወገኖችን ከጎዳ በማንሳት የማቋቋም ሥራ መከናወኑን ነው የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ መላኩ ባዩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

ባለፉት ሥድስት ወራትም በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና ሥራ ፕሮጀክት 4 ሺህ 550 እንዲሁም ከክልሎችና ከፌዴራል ከተማ አሥተዳደሮች በተገኘ በጀት 15 ሺህ 206 ወገኖችን ከጎዳና ላይ በማንሳት የተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ወደ መጡበት አካባቢና ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከጎዳና ላይ የተነሱ፣ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት የተለያዩ አገልግሎቶችን ያገኙ እና ወደ ቤተሰቦቻቸው (ማሕበረሰቡ) የተቀላቀሉ፣ የተዋሃዱና የተቋቋሙ ወገኖችን ቁጥር ከነበረበት 49 ሺህ 82 ለማድረስ ታቅዶ 54 ሺህ 288 ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርም ለሥራው ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራቱ ዕቅዱን ከታሰበው በላይ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version