Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ የተቀበሉ የመሬት ሊዝ አስተዳደር ሰራተኞች እጅ ከፍንጅ ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ የተቀበሉ የመሬት ሊዝ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጉዳይ ለመፈፀም 1 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ ሁለት የመሬት ሊዝ አስተዳደር ፅ/ቤት ሰራተኞች እና ተባባሪያቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቅንጅት ስራ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተገልጿል፡፡

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መስፍን በላቸው እንደገለፁት÷በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር የቦታ ርክክብና ክትትል ቡድን መሪ እና የሊዝ ማስተላለፍ ባለሙያ ናቸው፡፡

ሶስተኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ ለወንጀሉ ተባባሪ የሆኑ የሊዝ ማስተላለፍ ባለሙያው እህት ናቸው ተብሏል፡፡

የግል ተበዳይ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በሊዝ የገዙትን ቦታ ለመረከብ ሲመላለሱ ከቆዩ በኋላ የግንባታ ማስጀመሪያ ፈቃድ እንዲራዘምላቸው ለመጠየቅ አገልግሎት ፈልገው ወደ ክፍለ ከተማው አስተዳደር እንደሄዱ ተጠቅሷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ተገቢውን አገልግሎት መስጠጥ ሲጠበቅባቸው ቀጠሮ በማብዛት ሲያመላልሷቸው እንደነበር እና ጉዳዩን ለመፈፀም ገንዘብ እንደተጠየቁ የግል ተበዳይ መግለፃቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

“በሊዝ የተገዛው ቦታ መንገድ ዳር በመሆኑ እኛ ለምንፈፅምልዎት ጉዳይ የሚከፍሉን ገንዘብ ይጨምራል” የሚል መደራደሪያ ሃሳብ በማቅረብ ተጠርጣሪዎቹ 3 ሚሊየን ብር ጠይቀው እንደነበርም ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም ወደ 1 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ዝቅ እንደተደረገ የተገለጸ ሲሆን÷ከተጠየቀው ገንዘብ 1 ሚሊየን 200 ሺህ ብሩ የሊዝ ማስተላለፍ ባለሙያው ተጠርጣሪው እህት የባንክ ሂሳብ ውስጥ እንዲገባ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡

ከግል ተበዳይ በቀረበ አቤቱታ ፖሊስ የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል 200 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ተብሏል፡፡

Exit mobile version