Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለድህረ ሰብል ስብሰባ አመቺ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት ውስጥ የሚኖረው የአየር ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በመከናወን ላይ ለሚገኘው የድህረ ሰብል ስብሰባ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
 
በደቡብ አጋማሽና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች ምቹ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
እንዲሁም ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት ጥምር ግብርና ለሚያካሂዱት ለደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ለእንስሳት ልማትም ሆነ ለሰብሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።
 
በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚጠበቅ ነው የተመላከተው፡፡
 
በእነዚሁ አካባቢዎች ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንፃር ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡
 
በእነዚህ ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሃያማው እና ነፋሻማው አየር ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው አሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
 
በሌላ በኩል የበልግ ወቅትን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ለማዘጋጀት ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
 
በጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ የበጋው ደረቅ፣ ፀሀያማውና ነፋሻማው የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋል ተመላክቷል፡፡
 
ይሁንና በፀሀይ ኃይል ታግዘው ከሚፈጠሩት የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ የደመና ክምችት እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ተጠቁሟል፡፡
 
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይም በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገራችን ሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ሲዳማ ክልል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡
 
አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል፡፡
 
በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ምዕራብ አርሲ፣ አርሲ፣ የጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂና የቦረና ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
 
በተጨማሪም ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ዞኖች እንዲሁም አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) ቀላል መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡
 
የምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦራ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ፣ የምስራቅና የምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም ድሬዳዋና ሐረሪ፣ የመካከለኛው፣ የምስራቅ እና የደቡብ ትግራይ ዞኖች እንዲሁም ከአፋር ክልል ዞን 2፣ 4፣ 3 እና 5 ቀላል መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል።
 
በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ባሉት ቀናትም በምስራቅ አማራ፣ በመካከለኛው እና በምስራቅ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚስተዋል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version