Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ መሆኗ ለቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ስበት የጎላ አስተዋጽኦ አለው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ መሆኗ ለቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ስበት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ምሁራን ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪና መምህሩ ዱጋሳ ሙሉጌታ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈፀመችው ስምምነት ቀጠናዊ ልማትን የሚያፋጥንና ወደ ዓለም ገበያ የመውጫ መግቢያ ችግሯን የሚፈታ ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ በፍቃዱ ዳባ እንደገለጹት÷ ስምምነቱ የኢትየጵያን የኢንቨስትመንት ስበት ይበልጥ ተፈላጊ ያደርገዋል፡፡

የቀድሞው ዲፕሎማት ፕ/ር ብሩክ ሀይሉ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ የዓለም ሀይል አሰላለፍ እየተቀየረ መምጣቱ ሀገራት ለጋራ ጥቅም በጋራ እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት ስምምነትም ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጎለብት ነው ብለዋል፡፡

ትብብሩ በቀጣናዊ ትስስር ላይ ከምጣኔ ሀብት እስከ ወታደራዊ ጉዳዮች አቅምን የሚያጠናክር ነው ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ጥናት ተመራማሪው ንጋቱ አበበ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ስምምነቱ የጋራ ብልጽግናና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያፋጥን እንደሆነም ምሁራኑ ገልጸዋል፡፡

መሰል የሰጥቶ መቀበል ስምምነቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ምሁራኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ እና አሸናፊ ሽብሩ

Exit mobile version