Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሣደግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሣደግ በመንግሥት ስትራቴጅክ እቅድ ወጥቶ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የተሳካ ውጤት እያስገኙ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።

በኢኮኖሚ ልማት የመንግሥትን እቅድና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመንግሥት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግስት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅክ ዕቅድ ወጥቶ እየተሰራና ውጤትም እየተመዘገበበት ነው ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡

በሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ የእድገት ምንጭ ብዝኅ ዘርፍ እንዲሆን መደረጉ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷልም ነው ያሉት፡፡

የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ አይ ሲ ቲ እና ሌሎችም የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፎች የኢትዮጵያን እድገት በማሳለጥ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግርን ለማቃለልም በአጭርና መካከለኛ ጊዜ የግብርና ልማት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በበጋ የስንዴ መስኖ ልማት የተገኘው ምርት አስደናቂ መሆኑን ጠቁመው÷ የልማት ሥራው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

በዘንድሮው የበጋ ወቅት 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ የስንዴ አዝእርት በመሸፈን ከ117 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታልሞ እየተሰራ ነው ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የግብርና ምርታማነትን ለማሣደግም ዘመናዊ የእርሻ ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን በማቅረብ ለአርሶ አደሩ እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በሌማት ቱርፋት መርሐ-ግብር የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የዶሮ፣ ዓሳና የማር ምርቶች ላይ የተጀመረው ስራ ለበርካታ ዜጎች የገቢ አማራጭ እንዲፈጠር ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓት በመቀየር የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ አገራዊ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ስራውን የሚያግዝ ሲሉም አሰገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ለግብርና ምርታማነት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚሀኝም ነው ያመላከቱት በማብራሪያቸው፡፡

Exit mobile version