አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሀን ዜጎች ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰሱ የክልሉ የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና የልዩ ኃይል ኃላፊዎች በቀረበባቸው የክስ ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።
ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገመንግስትና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።
ችሎቱ በክስ መዝገቡ የተካተቱ 7ኛ እና 8ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱ ተከሳሾችን በሚመለከት በተከሰሱበት ድንጋጌ በነጻ አሰናብቷቸዋል።
አጠቃላይ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ተከሳሾች የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ ም/ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር፣ የቀድሞ የክልሉ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን እና የተለያዩ የፀጥታ አባላቶችን ጨምሮ አጠቃላይ 15 ነበሩ።
ከተከሳሾቹ መካከል ከ1ኛ እስከ 13ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ባጠቃላይ በተከሳሾች ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ከአራት ወር በፊት ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በዚህም በቀረበባቸው ክስ ላይ በጦርነት ጊዜ ንፁሃን ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን የጄኔቫ ቃል ስምምነት የፕሮቶኮል ድንጋጌን በመላተላለፍ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ1 ሀ/ለ፣ አንቀጽ 35 እንዲሁም አንቀጽ 270 ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎች መተላለፍ የሚል ነው።
ተከሳሾቹ በጋምቤላ ከተማ በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ በቀበሌ 03 በኩል በፌደራል ፖሊስ ካምፕ እና በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም በሌሎች ፀጥታ አካላት ላይ የከፈቱትን ድንገተኛ ተኩስ ተከትሎ በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ ማንነታቸው የተለዩ 35 ሰዎች እና ማንነታቸው ያልተለዩ ሌሎችም ንፁሃን ዜጎችን መረጃ ሰጥታችኋል በሚል ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ትዛዝ በመስጠትና በግድያው የተሳተፉ አሉ በማለት በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።
ተከሳሹቹ ከ1ኛ እስከ 13ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች የተመሰረተባቸው ክስ ዝርዝር በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊትን እንዳልፈጸሙ ጠቅሰው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች ቀርበው ይሰሙልኝ በማለት አጠቃላይ 37 ምስክሮች እንዳሉት ገልጾ የምስክር ቃል እንዲሰማለት ጠይቆ ነበር።
በፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ካስመዘገባቸው ምስክሮች መካከል ከ15 በላይ የምስክሮችን ምስክርነት ቃል አዳምጧል።
በዚህ መልኩ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃል ወደ ጽሁፍ በማስገልበጥ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት 11 ተሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ወንጀል መፈጸሙ መረጋገጡን ጠቅሶ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።
በመዝገቡ 7ኛ እና 8ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል አባላት በነበረው በኮ/ል አቶሬ ጉር እና በጋምቤላ የፖሊስ ኮሚሽን አባል የነበረው ረ/ሳጅን ቾድ ቤንግ የተባሉ ተከሳሾችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በቀረበባቸው ክስ ላይ በቂ ማስረጃ አለመሰማቱን ገልጾ በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል።
በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 14ኛ እና 15ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ ያላቸውን ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

