አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕር በር ማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ከሶማሊ ላንድ ጋር መፈረሙ ሀገራዊ ስኬታችን በድል እየደመቀ መሄዱን አመላካች ነው ሲሉ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታሪካዊ ነው የተባለውን የመግባቢያ ሠንድ በአዲስ አበባ መፈራረማቸውን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ስምምነቱ የሕዝቦችን ልማት እና ተጠቃሚነት ይበልጥ በማረጋገጥ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን የሚያደርግ ትልቅ ማሳያ ነው ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአንድ በኩል የውስጥና የውጪ ፈተናዎችን በመጋፈጥ በሌላ በኩል ለቀጣይ ትውልድ ስንቅ ሊሆን የሚችል ተስፋ ሰጪ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት ሀብት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል በመልዕክታቸው።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በኢንፎርሚሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች አመርቂ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

