Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮ-ቴሌኮም የልብ ህሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የሚውል ዲጂታል የድጋፍ ማሰባሰቢያ አማራጭ አዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ-ቴሌኮም ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የሚደረገውን ድጋፍ ቀላልና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ድጋፍ ማድረጊያ አማራጭ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

ኢትዮ- ቴሌኮም የዲጂታል የመርጃ አማራጮችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢትዮ- ቴሌኮም የኮሙኑኬሽን ዲቪዥን ዳይሬክተር ወ/ሮ አዜብ መለሰ÷ ኢትዮ- ቴሌኮም በሀገሪቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማቅለል ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ማህበራዊ ሃላፊነቱንም በመወጣት አጋርነቱን በተግባር እያሳየ ስለመሆኑ በመግለጽ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ለ1 ወር የሚቆይና ገቢው ለልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የሚውል የድጋፍ መርሐ ግብር እንዳዘጋጀ ተናግረዋል፡፡

መርሐ ግብሩ የኢትዮ- ቴሌኮምን የዩትዩብና የፌስ ቡክ ገጾችን ሰብስክራይብና ፎሎ በማድረግ በአንድ ሰው 30 ብር ወደ ማዕከሉ ገቢ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮ-ቴሌኮም ይፋ የሚያደርጋቸውን መተግበሪያዎችና መሠል ሁነቶችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች አንድ መረጃን በሚያጋራ ሰው 10 ብር ወደ ማዕከሉ ገቢ ይሆናል ነው ያሉት።

ለማዕከሉ ለገቢ ማሰባሰቢያነት እንዲውል ታስቦ በተዘጋጀው 6710 የነፃ መስመር በሚላኩ ድጋፎች ላይም እንዲሁ 10 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ሃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ ህሩይ አሊ እንደገለጹት÷ ማዕከሉ ላለፉት 35 ዓመታት የነፃ የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም በልብ ህመም ምክንያት የሚሰቃዩ በርካታ ህፃናት ጤናቸው እንዲመለስ በማድረግ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ለአንድ ወር የሚቆየውን ይህን የዲጂታል የድጋፍ መስጫ አማራጭ በመጠቀም እንደ ሁልጊዜው ቀና ትብብሩን እንዲያደርግ ዋና ስራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version