Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የፈረሙትን የመግባቢያ ያለልዩነት እንደሚደግፍ አስታወቀ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ያለ ልዩነት እንደሚደግፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ፣ በስምምነቱ ይዘትና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ አባላቱ በዝርዝር በመወያየት ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን አስታውቋል።

መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ህብረተሰብ የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡም የጋራ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

እኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጥር 01፣ ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የተገኝን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄድነው ስብሰባ :

1ኛ በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመውን ” መግባቢያ ሰነድ” በተመለከተ የስምምነቱን ማዕቀፍ ፣ዝርዝር ይዘቱን እና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ በዝርዝር ከተወያየን በኋላ ስምምነቱን ያለልዩነት የምንደግፍ መሆናችንን አረጋግጠናል::ከተግባራዊነቱ አንፃር የሚኖሩትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ስጋቶችን እና እድሎችን በዝርዝር መክረን ለስምምነቱ ውጤታማነት በጋራ በመቆም ሚናችንን ለመወጣት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም እናረጋግጣለን:: መንግስት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ህብረተሰባችን የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::

2ኛ. አካታች ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ስራው የደረሰበትን ደረጃ ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና በመፍትሄ አቅጣጫወች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናን አስመልክቶ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቀረበው ሪፓርትና ማብራሪያ ላይ ውይይት ካደረግን በኋላ ለምክክሩ ውጤታማነት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል:: በሂደቱ ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉም ጥሪያችንን እናቀርባለን:: ለምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬት እንቅፋት እየሆነ ያለውን የሰላምና የጸጥታ ችግር በመቅረፍ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ህዝባችን እንዲረባረቡ ጥሪ እናቀርባለን::

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
አዲስ አበባ
ጥር 02 ፣ 2016 ዓ.ም

Exit mobile version