Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከጎጃም ቀጣና ኮማንድ ፖስት ስምሪት የተቀበሉ አመራሮች ሥራ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጎጃም ቀጣና ኮማንድ ፖስት ስምሪት ተቀብለው በወረዳዎች የሕዝብ ለሕዝብ ሥራን ሲያከናውኑ የነበሩ አመራሮች የእስካሁን ሥራቸው ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።

የዞኑን አመራር የስምሪት ሪፖርት ለኮማንድ ፖስቱ ያቀረቡት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ÷ ዞኑ በወረዳዎች ተንቀሳቅሶ ሕዝቡን በማወያየት ሕብረተሰቡ ከሰላም ጎን እንዲሰለፍ ውጤት ተኮር ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ አመራርም በወረዳዎች የሕዝብ መድረኮችን በመክፈት የፅንፈኛውን ሴራና ፍላጎት በማስገንዘብ ሕብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

የጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ በበኩላቸው ÷ በየደረጃው ያለው አመራር ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ሆኖ በቁርጠኝነት በመሥራት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሕዝቡም ለሰላምና ፀጥታ ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ከመንግስት የፀጥታ ኃይል ጎን እንዲሰለፍ ጠይቀዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ/ር)÷ በጎጃም ቀጣና በአብዛኞቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ዳግም እንዲጀምር መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ከወረዳ እስከ ዞን ያለው የመንግሥት ሠራተኛ ወደ ሥራ ገብቶ ተመልሶ ሕዝቡን ማገልገልና ኃላፊነቱን መወጣት ጀምሯልም ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version