አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ አሁን ላይ በክልሉ 5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በሙሉ ወይም በከፊል አርብቶ አደር ሥራ እንደሚተዳደሩ አንስተዋል፡፡
እነዚህን በክልሉ 9 ዞኖች እና 45 ወረዳዎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻልም ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
መንግስት በተለይም ከለውጡ ወዲህ በአርብቶ አደሩ ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የአርብቶ አደሩን ሕይወት ማሻሻል የሚያስችሉ የመሰረት ልማት ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ለአብነትም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና ተቋማት፣ የትምህር ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን አንስተዋል፡፡
ለእንስሳት በቂ የመኖ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻልም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የአርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል እና ውጤታማ እንዲሆኑም ለአካባቢው የሚስማሙ የእንስሳት ዝርያዎችን የማላመድ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በክልሉ ለመስራት ከታቀዱት 73 “የፊና ፕሮጀክቶች” መካከል 35ቱ በ10 ቢሊየን ብር ወጪ በአርብቶ አደር አካባቢዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡