አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኩባ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳልቫዶር ቫልዴስ ጋር የሁለቱን ሀገሮች ሁለገብ ትብብር እና ወዳጅነት በሚመለከት ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ስለ ደቡብ-ደቡብ ትብብር፣ ጂኦ ፖለቲካል ፉክክር ምክንያት እየተዳከመ ስለመጣው የባለብዙ ወገን ዓለምአቀፍ ትብብር እና በአንድ ወገን ስለሚጣል ኢፍትሃዊ ማዕቀብ መክረዋል።
የሁለትዮሽ ትብብርን በሚመለከት በህብረተሰብ ጤና፣ በትምህርት እና በስኳር ኢንዱስትሪ ልማት በጋራ የመስራትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ትብብርን እና መደጋገፍን አጠናክሮ ለመቀጠል የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር በቅርብ ጊዜ እንዲካሄድ በውይይታቸው ወቅት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።