Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት እቅድ ሀገራት ሊደግፉት እንጂ ሊነቅፉት አይገባም – አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የሰጥቶ መቀበል የትብብርና በጋራ የመልማት እቅድ ሀገራት ሊደግፉት እንጂ ሊነቅፉት እንደማይገባ በአሜሪካ፣ ቻይና እና ካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎትና የወደብ ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ120 ሚሊየን በላይ ህዝብ ይዛ ሰፊ የልማትና የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ላለች ሀገር የባህር በር በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀይ ባህር አካባቢና አጠቃላይ በቀጣናው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን ለመወጣትም የባህር በር እንደሚያስፈልጋት አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የባህር በር ስምምነት ከሀገራዊ የጋራ ጥቅም ባለፈ አህጉራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት መርህን በተከተለ መልኩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ስምምነቱን የጥላቻና አለመረጋጋት ምክንያት የሚያስመስሉ አካላት እየተሳሳቱ መሆኑን በመረዳት እውነታውን በቅጡ ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አካሄድ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ፤ በጋራ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን መርሐ ያደረገ እንዲሁም የሀገርን ክብርና ጥቅም የሚያስከብር መሆኑንም አስረድተዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጋራ የመልማት አላማ መሰነቁን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የትብብርና በጋራ የመልማት አላማ የቀጣናውም ይሁን የዓለም ሀገራት ሊደግፉት እንጂ ሊነቅፉት አይገባም ነው ያሉት።

በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ÷ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርሕ የልማት ትስስርን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሰረተ ልማት ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦትም ጎረቤት ሀገራት እንዲጠቀሙ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ገልጸው÷ የባህር በር ስምምነቱም ተመሳሳይ አላማ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።

Exit mobile version