Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት የሰረቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለውና ለውሃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚያገለግል ንብረት የሰረቁ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀሙት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አርባ ዘጠኝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ ነው ተብሏል፡፡

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የበሻሌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ደበበ ከለላው እንደገለጹት÷ በመጋዘን ውስጥ ተቀምጦ የነበረ የፕላስቲክ ቧንቧ መገጣጠሚያ ኤልቦ የተሰረቀው ንብረቱን እንዲጠብቁ ሃላፊነት በተሰጣቸው ግለሰቦች ተባባሪነት ነው፡፡

የዋጋ ግምቱ 21 ሚሊየን 959 ሺህ 600 ብር የሆነውን ንብረት ሌሊት ከሰረቁ በኋላ በአጥር ከግቢው በማውጣት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-A 55424 አ.አ በሆነ ተሽከርካሪ ለመጫን ሲዘጋጁ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ሶስት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ይዟል ተብሏል፡፡

ንብረቱን ለመጠበቅ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመዘንጋት ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ተባባሪ የነበሩ ሌሎች አራት ግለሰቦችም ተይዘው የምርመራ ስራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version