አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ከ147 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የ2016 የተፋሰስ ልማት ስራዎች በዛሬው ዕለት በክልሉ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ መካሄድ ጀምሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻ ጣሰዉ በወቅቱ እንዳሉት÷ የአፈር መሸርሸር በክልሉ ምርታማነት ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡
በመሆኑም በክልሉ የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ በአፈር መሸርሸር የተፈጠረውን የአፈር አሲዳማነትን ማከም የሚያስችል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
25 ቀናት በሚቆየው የተፋሰስ ልማት ስራ ማኀበረሰቡ የተለመደዉን ተሳትፎውን በማጠናከር የተያዘውን እቅድ እንዲያሳካ ጥሪ አቅረበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው÷ በተፋሰስ የልማት ስራው ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ህዝቦች ይሳተፉበታል ብለዋል፡፡
ለተፋሰስ ልማት ስራዎች የልየታና የዲዛይን ስራዎች መከናወናቸዉን ገልጸው÷ በዚህም 1 ሺህ 300 ንዑስ ተፋሰሶች የተለዩ ሲሆን ከ147 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ይለማል ብለዋል።
በቀጣይ በሚከናወኑ ስራዎችም በመደበኛነት ከሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን የማደስ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡
ከተፋሰስ ልማት ስራዎች ጎን ለጎን ለክረምት የአረንጓዴ ችግኝ ተከላ የሚዉሉ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ስራዎች እየተከናወኑ የሚገኙ ሲሆን 70 ሚሊዮን ጉድጓዶች ተቆፍረው ዝግጁ እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡
በቢቂላ ቱፋ