Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ1 ሚሊየን ብር በላይ፣ ዶላርና የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ አከማችቶ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ሚሊየን ብር በላይ፣ በርካታ ዶላርና የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ በመኖሪያ ቤቱ በሕገ-ወጥ መንገድ አከማችቶ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ነዋሪነቱ በወረዳ 4 ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ያከማቸ መሆኑን ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጡን ተከትሎ ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትእዛዝ በማውጣት በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት በዛሬው ዕለት ፍትሻ አካሂዷል፡፡

በዚህም 1 ሚሊየን 199 ሺህ 290 ብር፣ 26 ሺህ 405 የአሜሪካ ዶላር፣ 5 ሺህ 100 የካናዳ ዶላር፣ 34 ሺህ 150 ዮሮ እና 1 ሺህ 635 የሳዑዲ ሪያል እና 27 ጥይት በኤግዚቢትነት መያዙን ጠቅሷል፡፡

መምሪያው በብርበራ ወቅት ፈቃድ አለው የተባለ ሽጉጥ መያዙን ገልጾ÷ የሽጉጡን ሕጋዊነት እያጣራ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ እና ለወንጀል መፈፀም መንስኤ በመሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

ሕብረተሰቡም የወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን በመጠቆም እና መረጃ ለፖሊስ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል፡፡

Exit mobile version