Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይጠናከራሉ -ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚጠናከሩ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መግለጫ በአሥር ቀናት ውስጥ በደቡብ ምዕራብና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚስተዋለው አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት በስተቀር በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይቀጥላል ብሏል።

ያም ሆኖ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚጠናከሩ ጠቁሟል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አስታውቋል።

በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት በተለይም በምዕራብ መካከለኛውና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አመላክቷል።

በእነዚሁ ቀናት ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ የሰሜን፣ የምዕራብና የምስራቅ ሸዋ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙም የትንበያ መረጃዎች መኖራቸውን አስታውቋል።

አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ የደቡብና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ የባህር ዳር ዙሪያም በተመሳሳይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።

በተመሳሳይም የሰሜንና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የዋግህምራ ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የምስራቅ የመካከለኛውና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚኖራቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ በትንበያው አመላክቷል።

ከጋምቤላ ክልል የማጃንግና ጥቂት የአኝዋክ ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የመካከለኛው ጎንደርና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውም ተገልጿል።

የባሌ፣ የምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ እንዲሁም የሀረሪና ድሬዳዋ፣ ከሰማሌ ክልል የሲቲና ፋፈን ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ዞን 2 እና ዞን 4 እንዲሁ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version