Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሥራ ላይ ልምምድ ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የላቀ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ ላይ ልምምድ ለወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የላቀ ድርሻ እንዳለው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ፡፡

“ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም” ሁለተኛ ዙር ትግበራ በሐዋሳ ከተማ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ አቶ ንጉሡ ጥላሁን÷ የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ለወጣቶች የተሟላ ክህሎት በማላበስ ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ድርሻው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ ላይ ልምምድ ከመሰማራታቸው በፊት የህይወት ክህሎት፣ የሥራ ፈጠራና ሙያዊ ክህሎት ሥልጠናዎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አማካኝነት ማግኘታቸው ለሥራ ገበያው ራሳቸውን ለማዘጋጀት እንዳስቻላቸውም አስረድተዋል፡፡

ወጣቶቹ ያደረጉት ቅድመ ዝግጀትም በተሠማሩበት የሥራ ላይ ልምምድ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር ጉልህ አበርክቶ ነበረው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም በሐዋሳ ከተማ በ110 ድርጅቶች ውስጥ ለ6 ወራት የሥራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ 868 ወጣቶች ወደ ሥራ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

Exit mobile version