Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአምራች ኢንትርፕራይዞች ለ74 ሺህ 989 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በአምራች ኢንተርፕራይዞች ለ74 ሺህ 989 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱፈታህ የሱፍ እንዳሉት፥ በግማሽ ዓመቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻል የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል።

በዚህም ለአምራች ኢንትርፕራይዞች 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

1 ሺህ 493 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች መቋቋማቸውን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡

በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተመርተው ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶችም 17 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም አንስተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በአምራች ኢንተርፕራይዞች ለ74 ሺህ 989 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል 37 ሺህ 541 ቶን በላይ የግብዓት ትስስር መፈጠሩን ጠቁመው፥ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦ ችግር፣ የመስሪያ ቦታ እጥረት እና የሃይል አቅርቦት ማነስ የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደነበሩም አስረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version