አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማፋጠን ሕብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ፡፡
በቡሌ ሆራ ከተማ አስተዳደር እና ምዕራብ ጉጂ ዞን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ፡፡
በውይይቱ መድረኩ የተገኙት አቶ ጌታሁን አብዲሳ ÷ኢትዮጵያ ተበተነች ሲሉ ይበልጥ እንደ አለት እየጠነከረች በችግር ውስጥም ሆና እድገት እያስመዘገበች መምጣቷን ተናግረዋል፡፡
የሀገራችንን ብልጽግና ለማፋጠንም ሕብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
የጸጥታ ችግር ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ መምጠቱን ጠቁመው÷ ችግር ፈጣሪዎችን ተባብረን ከውስጣችን ማውጣት አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ እድገቷን የጎተቱ ብዙ ፈተናዎችን አልፋ እዚህ መድረሷን ጠቅሰው÷ ፈተናዎችን ያለፈችው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መመከት ስለቻለ ነው ብለዋል።
ብዙ ቢጥሩም ያልተሳካላቸው የሕዝቡ ስር የሰደደ ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ስላለ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች መሆኗን የዚህ ዞን ሃብት ብቻ ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ÷ ከእኛ አልፎ ለሌሎች የበቃ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩን አውስተዋል።
በአንጻሩ ሰፊ አምራች ሃይል እና ሰፊ መሬት ያለን ቢሆንም ዘመናት የተሻገረ የድህነት ችግርን ግን መላቀቅ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
እጋጠመን ያለው ችግር ከማጣት የመነጨ እንዳልሆነ ያለን ሀብት ምስክራችን ነው ያሉ ሲሆን÷ስለዚህም ችግሮቻችንን አውቀን፣መነሻውን ለይተን መፍትሄ ለመስጠት አላማው ያደረገ ውይይት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማርታ ጌታቸውና ለሊሴ ተስፋዬ