አዲስ አበባ፣ የካቲት 04፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመጀመሪያውን ምዕራፍ አጠናቆ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ፤ እስካሁን በተሰራው ስራ የተሳታፊዎች ልየታን ጨምሮ ለምክክሩ ሂደት ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጿል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓረአያ÷ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች 1 ሺህ 400 ወረዳዎችን ያካለለ ውይይቶች መደረጉን አንስተዋል።
በትግራይ ክልል እና በአማራ እንዲሁም በኦሮሚያ ጥቂት ቦታዎች የቀሩ ስራዎች በቀጣይ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።
በቀጣይ ምዕራፍም በክልሎች፣ በፌዴራል ደረጃ እና በውጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች አጀንዳ የመሰብሰብ ስራ እንደሚሰራም ተመላክቷል።
አጀንዳ መሰብሰብ ከተጠናቀቀ በኋላ አጀንዳዎች ሁሉ ወደ ዋናው ፅህፈት ቤት ገብቶ የአጀንዳ መረጣ ይደረጋል ተብሏል።
የአጀንዳ መረጣው ሲያበቃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ወደ ፊት በማምጣት ምክክር ወደ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በሂደቱ ሁሉንም አካል አሳታፊና አካታች የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓረአያ ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ 8112 ነፃ የስልክ ጥሪ እና አጭር የጽሑፍ መልዕክት መቀበያ አገልግሎት ማዕከል ወደ ስራ ማስገባቱን ይፋ አድርጓል።
የነፃ መስመሩን በመጠቀምም ማንኛውም ሰው አጀንዳን ጨምሮ የተለያዩ ሃሳቦችን ለኮሚሽኑ መስጠት ይችላል ተብሏል።
የአገልግሎት ማዕከሉ ለኮሚሽኑ ስራ ውጤታማነት የራሱን ድርሻ እንደሚወጣም ይጠበቃል ተብሏል።
በተጨማሪም https://ethiondc.org.et ድረ ገፅን ሥራ ማስጀመሩም ተገልጿል።
በታሪኩ ለገሰ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!