አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአደገኛ እፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ናይጄሪያዊ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።
ቺቡኬ ዳንኤል የተባለው ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 525/1/ለ/ ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ አደገኛ እፅ በማዘዋወር ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቅጣት ተላልፎበታል።
የፍህትህ ሚኒስቴር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ መነሻውን ናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ አድርጎ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም ወደ ሞምባስ ከተማ ለማዘዋወር ሲል መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በተደረገው ፍተሻ 7 ሺህ 27 ግራም ኮኬይን የተባለ አደገኛ እፅ ይዞ ተገኝቷል።
ተከሳሹ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ በችሎት ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ወንጀሉን እንደፈጸመ አምኖ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል በህግ የተከለከለውን በአደገኛ እፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል፡፡
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት በህግ የተከለከሉ እፆችን የማዘዋወር ወንጀል የፈፀመውን ተከሳሽ ያርማል በማለት በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እና 40 ሺህ ብር እንዲቀጣ መወሰኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡