አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ጥያቄዎችን አውቆ ችግሮችን ለመፍታት በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት አሰናጅነት የተካሄዱ ውይይቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ፡፡
ባለፉት ቀናት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግሥት አዘጋጅነት ሕዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
ውይይቶቹም ለሕዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ ረሽድ ተናግረዋል፡፡
የኅብር ፓርቲ ሊቀመንበር ግርማ በቀለ በበኩላቸው÷ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችን እና ፍላጎቶችን ለማወቅ የውይይቶቹ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት የሚሄድበት መንገድም ውይይቶቹን ፍሬያማ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት እና ታጣቂ ኃይሎች መካከልም እውነተኛ ድርድር እንዲደረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በሂደቱም ሁሉም አካል የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገር ጠቃሚ ታሪክ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል፡፡
ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ ሕዝባዊ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት አመራሮቹ÷ ጥያቄዎቹ ተግባራዊ መልስ ሲያገኙ ለዘላቂ ሰላም ከፍተኛ ጥቅም ያበረክታል ብለዋል፡፡
በሰሎሞን ይታየው