Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለችው ግለሰብ በእስራት ተቀጣች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለችው ግለሰብ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ41 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተቀጣች።
 
ደመቀች ማጉጄ አቤቱ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27 (1) እና በሰው የመነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 11 (1) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባታል።
 
የፍትህ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ጥፋተኛ የተባለችው ግለሰብ ስድስት ክሶች ቀርበውባታል፡፡
 
በውል ባልታወቀ ቀን ህዳር ወር 2014 ዓ.ም ስድስት የግል ተበዳዮችን ዮርዳኖስ ሀገር ሥራ አስቀጥራችኋለሁ በማለት ለምርመራ፣ ለቪዛ፣ ለስልጠና እና ለፓስፖርት በሚል ከእያንዳዳቸው እስከ 39 ሺህ 500 ብር በአጠቃላይ 182 ሺህ 500 ብር መቀበሏም በክስ መዝገቡ ተመላክቷል፡፡
 
በዚህም ታህሳስ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ዮርዳኖስ ስለምትሄዱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቀድማችሁ መድረስ አለባችሁ ብላ ካደረሰቻቸው በኋላ ግብረ-አበሯ የሆነ ግለሰብ የበረራ ትኬት ይዞ እየመጣ ነው በሚል ሳይመጣ ሲቀር ከምሽቱ 5 ሰዓት ሲሆን ነገ ትሄዳላችሁ አሁን አልጋ ይዘን ታድራላችሁ በማለት እየተመለሱ እያለ ከሌሊቱ በግምት 7 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ ፖሊስ በጥርጣሬ እንደያዛቸው የዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል።
 
ተከሳሽ በፈፀመችው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሙከራ ወንጀል ተከሳ ፍርድ ቤት ቀርባ የወንጀሉ ድርጊት ፈጻሚ መሆኗን አምና ጥፋተኛ መባሏን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 እርከን 34 መሰረት ተከሳሽ በከባድ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሙከራ ወንጀል ጥፋተኛ ናት በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡
 
ፍርድ ቤቱም ሦስት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ ተከሳሽን ከአድራጎቷ ያርማታል፣ ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ41 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም ለ5 ዓመት ከሌሎች ማህበራዊ መብቶች እንድትታገድ ወስኗል፡፡
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version