Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከትናንት ጀምሮ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉ ይታወቃል፡፡

ይህን ተከትሎም የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የዛሬውን ውሎ 44ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ  የአስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ካጠናቀቁ በኋላ የዓድዋ ድል መታሰቢያውን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀመት፣  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ለጎብኝዎችም በዓድዋ ጦርነት የቀደሙ አባቶች ለነጻነት ስለከፈሉት መስዋዕትነት፣ የትግል ሂደት እንዲሁም ስለ ዓድዋ ድል መታሰቢያ አጠቃላይ ይዘት በተለያዩ ቋንቋዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡

አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም÷ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ተሻግሮ በዓለም የተስተጋባ አኩሪና የጋራ ድላችን ነው ብለዋል፡፡

ዓድዋ የዓለምን ሕዝብ አመለካከትና አስተሳስብ ጭምር መቀየር የቻለ ድል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦች የትግል አርማና የመንፈስ ጥንካሬ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህንም በጉብኝታቸው ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡

መታሰቢያነቱም ለኢትዮጵያውያን  ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦች እንዲሁም ለነፃነታቸው ለታዋደቁ አፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ድሉን የሚዘክር መታሰቢያ መገንባቱ መጭው አፍሪካዊ ትውልድ ጭምር ሲመለከተው ነፃ ሀገር ስለመረከቡ የተከፈለውን ዋጋ እንዲረዳ  ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በበኩላቸው÷ ስለ ዓድዋ ድል በጽሑፍ በተለያዩ መንገዶች የሚያውቁትን በዚህ መልኩ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ጠቅሰዋል፡፡

መታሰቢያውም ታላቁን የዓድዋ ድል በሚመጥን ደረጃ ልክ ተገንብቶ ለዕይታ በመብቃቱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመራኦል ከድር

Exit mobile version