Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በድሬዳዋ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፣ የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ጸጋዬ ማሞ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፈቲያ አደን እንዲሁም የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጨምሮ ወጣቶችና ሴቶችም በውይይት መድረኩ ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ከንቲባ ከድር ጁሀር፥ የህዝብን ችግር በመፍታት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር ከነዋሪው ለሚነሱ ጥያቄዎችም ተገቢ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስራ ለመስራት ውይይቱ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ያስመዘገባቸውን መልካም ውጤቶች በማስቀጠልና ከህዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎችም መፍትሄ በመስጠት ህዝብ የጣለብንን አደራ ለመወጣትም ቁርጠኛ ለመሆን የሚያግዝ ውይይት እንደሆነም ነው የገለጹት።

በህዝቦች መካከል መግባባት እና ወንድማማችነትን በማሳደግ ረገድም ትልቁን ስራ በማከናወን የነገዋን የተሻለች ሀገር ለማቆም መሰል ውይይቶች ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ችግር ፈቺ አቅጣጫና ስልትን በመከተል የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶች የሚል ሰነድ ያቀረቡት በብልጽግና ፓርቲ የአስተዳደሩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ኢብራሂም የሱፍ፤ ከመልካም አስተዳደር እስከ ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ እንዲሁም የገበያ መረጋጋትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ተግባራትን በስፋት ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

ባህላዊ የግጭት አፈታትን በመተግበር ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቀነስ መሰራቱን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ31 ሺህ 600 በላይ የስራ እድል መፈጠሩን እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በይስማው አደራው

#Ethiopia #DireDawa

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version