አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ።
መድረኩ “ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።
በመድረኩ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍስሐ ይታገሱ እና የሶማሌ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱራህማን አህመድን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷ የሶማሌ ክልል ከለውጡ በፊት በበርካታ የልማት ዘርፎች ተቋዳሽ እንዳልነበር ገልጸው፤ ከለውጡ ወዲህ ግን ክልሉ በሰላም፣ በመልካም አስተዳደር እና በልማት ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጀመረው የለውጥ ጉዞ በርካታ ስኬቶች ቢኖሩም አሁንም ግን ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ውይይትም ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመሸጋገር ህዝባዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የሀገርን ብልጽግና ለማፋጠን ያግዛል ነው ያሉት።
በውይይቱ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የተለያዩ ጥያቄዎች አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተገልጿል ።
“ሃብትን የመፍጠር ጉዟችን ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ሁሉን አቀፍ የህዝብ ተሳትፎ ለብልፅግና ጉዟችን ስኬታማነት” በሚል ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ
ቀርቧል፡፡
በዛሬው ዕለት በሶማሌ ክልል ከቀብሪደሃር ከተማ በተጨማሪ በጅግጅጋ፣ በደገሃቡር እና በጎዴ ከተሞች ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።
በመሳፍንት እያዩ